//
Askwala

askwalaApr 14, 2019 at 02:52 PM

መንግሥት የስኳር ኮርፖሬሽንን ወደ ግል ለማዛወር የሚረዳ የቅድመ መረጃ ሰነድ ይፋ አደረገ

Informer: Wegen, from Business category

ገንዘብ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ያዘጋጀው የመረጃ መጠየቂያ ሰነድ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚሠራጭ አስታወቀ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዩ ሮባ ጋር በመሆን በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ወደ ግል ከሚዛወሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ እንደመሆኑ፣ መንግሥት ይህንን ተቋም ወደ ግል ለማዛወር የሚያስችሉትን ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደሩ 13 ፕሮጀክቶች ቢኖሩም፣ ከአቅሙ በላይ እንደሆኑበትና ኮርፖሬሽኑም ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ወደ ግል ማዛወሩ ግድ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ ይህንን ተከትሎም የኮርፖሬሽኑን ሀብትና ዕዳዎች ግመታና ዋጋ ማውጣት ሥራዎች እንደተካሄዱና አሁንም እየተካሄዱ እንደሚገኙ፣ ሚኒስትር ዴኤታውና ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

የገበያ መረጃ ሰነድ ዝግጅቱን በተመለከተ ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፣ ሰነዱ ለመነሻ የተዘጋጁ 15 ዋና ዋና ጥያቄዎችን በማካተት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መረጃዎቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን እንዲገልጹ እንዲስችሏቸው ሆነው የቀረቡ ናቸው፡፡ ይህም ሆነ ባለሀብቶቹ ሊኖሯቸው የሚችሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶችንም እንደ ፍላጎታቸው ማካተት የሚችሉበት ሰነድ ነው ብለዋል፡፡

ሰነዱ ከሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኒስቴሩ ድረ ገጽ ለመላው ዓለም እንደሚለቀቅ ያስታወቁት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ሰነዱን በመሙላት አስፈላጊ መረጃዎችን ለመስጠትና ጥያቄዎችንም ለማቅረብ እንዲችሉ እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰነዱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላላ መረጃ የማሳወቅና የመጠየቅ ሒደቱ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

ይህንን ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈለገው ባለሀብቶች ኮርፖሬሽኑን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መግዛት ቢፈልጉ፣ ካሉት 13 የስኳር ፕሮጀክቶች ምን ያህሉን ሊገዙ እንደሚችሉ፣ ወይም ከመንግሥት ጋር በሽርክና መሥራት ቢፈልጉ፣ ወይም ደግሞ በኮንትራት ስምምነት መግባት ቢፈልጉ እንዲህ ያሉትን መረጃዎች ለማወቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በርካታ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ለማዛወር ማቀዱን ይፋ ካደረገ ከበርካታ ወራት ቆይታ በኋላ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ቅድሚያ ሆኗል፡፡ መንግሥት ለስኳር ዘርፉ ለምን ቅድሚያ ሰጠ በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ደኤታው፣ በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር ያሉትን ሀብትና ይዞታዎች ማወቅ በመቻሉና ፕሮጀክቶችን ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወሩ ቀላል ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሌሎቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጥናት እየተደረገባቸው እንደሚገኙና በአንዳንዶቹ ላይ ማስተካከያ የሚፈልጉ ሥራዎች በመኖራቸው፣ ቅድሚያውን ስኳር ኮርፖሬሽን እንደወሰደ ተጠቅሷል፡፡ የኢነርጂ ዘርፉን የሚመራው ተቋም ለአብነት ወደ ግል ለመዛወር ከመዘጋጀቱ በፊት ብዙ መስተካከል ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ ይህም ይባል እንጂ ለሁሉም መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል የሚዛወሩበት አካሄድ ላይ ዝርዝር ሒደቱን የሚገዙ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በቅርቡ የተሾሙት አቶ ወዩ ሮባ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ ወደ ግል መዛወሩ ወይም በሥሩ የሚገኙ ፋብሪካዎች ለሽያጭ መቅረባቸው ከሥጋት ይልቅ ትልቅ አቅምና ውጤት እንደሚገኝበት እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ከፍተኛ መጓተት ከታየባቸው ውስጥ የበለስ ስኳር፣ የኦሞ አንድ፣ የኦሞ አምስትና የወልቃይት ፕሮጀክቶችን ወቅታዊ ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

ለበለስ ስኳር ፕሮጀክት አማካሪዎች ባጠኑትና የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ባየው ግምገማ መሠረት፣ ፕሮጀክቱ በስምንት ወራት ውስጥ መጠናቀቅ የሚችልበትን የግንባታ ስምምነት ከቻይና ኩባንያ ጋር መፈራረሙንና ሥራው መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ የኦሞ አንድ ስኳር ፕሮጀክትም በአማካሪ ተጠንቶ፣ የዲዛይንና የስፔስፊኬሽን ሥራዎቹም እንደተገመገሙ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ዓይነት መጓተት ከእንግዲህ እንደማይኖር ያስታወቁት አቶ ወዩ፣ ኮርፖሬሽኑ ወደ ግል ቢዛወር የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ ተስፋቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በወሰዳቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ሳቢያ የደረሰው የተንዛዛና የተጓተተ ከመሆን አልፎ፣ ከፍተኛ የገንዘብና የፕሮጀክት ወጪ አስተዳደር ችግሮች በመከሰታቸው የ77 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ፈተና እንደገጠመው ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ወዩና አጋሮቻቸው እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

Info source: Reporter


ONLINE E-BOOKS

Online E-books, Textbooks and related materials.